Sunday, April 19, 2015

በሊቢያ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ የተፈጸመው ግድያ የኢትዮጵያ መንግሥት በጽኑ አወገዘው

(አዲስ አበባ ሚያዚያ 11/2007))-- አይ.ኤስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን በሊቢያ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ 'ፈጽሜዋለሁ' በሚል ዛሬ በቪዲዮ ያሰራጨውን ዘግናኝ የግድያ ተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት በጽኑ አወገዘ።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አሸባሪዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ይህን መሰል የጭካኔ ተግባር ኢትዮጵያ በፅኑ ታወግዛለች።

ከመነሻው ጀምሮየኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ኃይማኖታዊ አክራሪነትና ሽብርተኝነት እየተዋጉና እየታገሉ መምጣታቸውን ሚኒስትሩ አስታውሰዋል። በዚህም የአገሪቱን ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት በአስተማማኝ ማረጋገጥ መቻሉን በመግለጽ።

የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዛሬ ባሰራጩት ዘገባ አሸባሪ ቡድኑ ግድያ ፈጸመባቸው የተባሉት ስደተኞች በእርግጥም ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማረጋገጫ እንዳልሰጠ ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት። "የአሸባሪ ቡድኑ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ኢትዮጵያውያን ቢሆኑም ባይሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት በንፁሃን ላይ የሚፈፀም የዚህ ዓይነቱ አሰቃቂና ዘግናኝ የሽብር ድርጊት አጥብቆ ያወግዛል" ብለዋል።

በሊቢያና በአካባቢው አገራት የሚኖሩ ዜጎች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና የቡድኑ እንቅስቃሴ በተጠናከረበት አካባቢ ምንም ዓይነት ዝውውር እንዳያደርጉ አሳስበዋል።

መንግሥት ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለው እንደሆነ አቶ ሬደዋን ገልጸው በሊቢያና የአሸባሪነት ጥቃት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ብሎም ወደ አገራቸው ለመመለስ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል። በመሆኑም በሊቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በግብጽ ካይሮ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ግኑኝነት እንዲፈጥሩ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  

No comments:

Post a Comment