Wednesday, January 21, 2015

ዘጠኝ ተጨማሪ የህዝብ ማጓጓዣ ባቡሮች ወደ አገር ውስጥ ገቡ

(ጥር 13/2007, (አዲስ አበባ))--ዘጠኝ ተጨማሪ የህዝብ ማጓጓዣ ባቡሮች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽ ገለጸ፡፡



የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጄ ተፈራ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በቻይና በመመረት ካሉ 41 ባቡሮች ውስጥ 19ኙ አዲስ አበባ ገብተው በመገጣጠም ላይ ናቸው። ቀሪዎቹ 22 ባቡሮች በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ ገብተው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል ።

በቻይና የባቡር ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እየተገነባ ያለውና 34 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር መስመር በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ሲሆን ባቡሩ ደግሞ በሰዓት 80 ኪሎ ሜትር እንዲያጓጉዝ ዲዛይን የተደረገ ነው፡፡ ባቡሩም ስራውን ሲጀምር በሰዓት ከ20 እስከ 30 ኪሎሜትር የሚጓዝ ሲሆን በአንድ ጊዜ ከ200 በላይ ሰዎችን ማጓጓዝ አቅም ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

ባቡሮቹ በቃሊቲ ዲፖ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የመገጣጠም ስራቸው እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። በመዲናዋ እየተገነባ የሚገኘውም የባቡር መሳፈሪያ ጣቢያዎች ግንባታ ከ86 በመቶ በላይ መጠናቀቁንም የገለጹት ኃላፊው ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ 39 የመሳፈሪያ ጣቢያዎች ይኖሩታል፡፡

ጣቢያዎቹ በመሬት ውስጥ ለውስጥ፣ ከፊል መሬት ላይና በድልድይ የተገነቡ መሆናቸውንና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ የግንባታው ሂደትም የደረጃዎቹ ስራ አልቆ ሼዶችን የመግጠም ስራ ላይ የደረሰ ሲሆን የግንባታው ሂደትም አለማቀፍ የጥራት መስፈርትን አልሟቶ የተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

በመጪው የካቲት ወር የሙከራ ስራውን ከቃሊቲ አካባቢ ለመጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራው መጠናቀቁን አብራርተዋል። ሰዎችም ሆነ እንስሳት ወደ ባቡሩ መተላለፊያ በቀላሉ እንዳይገቡ አጥሮችና የትራፊክ መብራቶች ተከላ በመከናወን ላይ ነው ብለዋል።                                                                     

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አሁን ያለው የትራንስፖርት እጥረት በመቅረፍ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ፈጣን፣ አስተማማኝና ምቹ የህዝብ ትራንስፖርት ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ማቅረብ ያስችላል ብለዋል። በተጨማሪም ባቡሮቹ የአካባቢ ብክለትን የሚቀንሱ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 475 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን 85 በመቶው ከቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር፤ ቀሪው 15 በመቶ ደግሞ  በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡


Related topics:
አስር ዘመናዊ ባቡሮች አዲስ አበባ ገቡ

No comments:

Post a Comment