Thursday, January 15, 2015

በኢቦላ ተጠርጥሮ ክትትል ሲደረግበት የቆየው ኢትዮጵያዊ ትናንት አረፈ

(ጥር 7/2007, (አዲስ አበባ))--በዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቀጥሮ ሴራሊዮን ሲሰራ የቆየ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ አገር ውስጥ ከተመለሰ በኋላ በኢቦላ ተጠርጥሮ ህክምና ሲደረግለት ቢቆይም ትናንት ጠዋት ማረፉንና የግለሰቡ ህመም ግን የጭንቅላት ወባ ሆኖ መገኘቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አስታወቁ። በፈቃደኝነት ወደ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ የተላኩ 189 ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች ስልጠናቸውን ጨርሰው ሥራ መጀመራቸውን አመለከቱ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ትናንት በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ግለሰቡ በኢቦላ ህመም ተጠርጥሮ በአግልሎ ማከሚያ ማዕከል የህክምና ክትትል ሲደረግለት ቆይቷል። ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀው ላቦራቶሪ በተደረገው የኢቦላ የደም ምርመራ ውጤት መሰረትም ግለሰቡ ከኢቦላ ነፃ መሆኑ ተረጋግጧል።

ይኸው ግለሰብ ወደ አገር ውስጥ በገባ በ15ኛው ቀን ትኩሳት እንደታየበትና አቅሉንም እንደሳተ (ኮማ ውስጥ እንደገባ) የገለጹት ሚኒስትሩ፤ «ኢትዮጵያ ለኢቦላ ባዘጋጀችው ላቦራቶሪ በተደረገው የደም ምርመራ ህመሙ የጭንቅላት ወባ (ፋልሲፓረም ወባ) ሆኖ ተገኝቷል» ብለዋል።

በላቦራቶሪው ውጤት ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ለመሆን ሲባልም የደም ናሙናው አሜሪካ ሀገር ወደ ሚገኘው የሲ ዲ ሲ ላቦራቶሪ ትናንትናውኑ መላኩንና ውጤቱም በ72 ሰዓት ውስጥ እንደሚታወቅ ጠቁመው፤ ለህዝቡም ይፋ እንደሚደረግም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

በግለሰቡ ላይ የተገኘው የጭንቅላት ወባ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ትናንትና ማረፉን ያስታወቁት ዶክተር ከሰተብርሃን፤ «ከግለሰቡ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ቤተሰቦቹና የቅርብ ጓደኞቹ በሙሉ ተለይተው መታወቃቸውን እንዲሁም ወደ አሜሪካ የተላከው የደም ናሙና ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ግለሰቦቹ ከማንም ጋር እንዳይገናኙ በማለት በቤት ውስጥ ክትትል እየተደረገባቸው ነው» ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻም፤ ከግለሰቡ ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉት ሰዎች ሁሉ በአንደኛ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ተለይተው የተቀመጡ ሲሆን፤ ሁሉም በቀን ለሁለት ጊዜ የኢቦላ ምርመራ እየተደረገላቸው ይገኛል። ግለሰቦቹም ለዚህ ፈቃደኛ ሆነው እየተባበሩ ይገኛሉ።

በተያያዘ ዜናም ወደ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ በፈቃደኝነት የተላኩ 189 ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት ስልጠናቸውን ጨርሰው ሥራ መጀመራቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

እስካሁን ድረስም ሁሉም ባለሙያዎች በጥሩ የጤንነትና የሥራ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ዶክተር ከሰተብርሃን፤ የሥራ ውሏቸውንና አጠቃላይ ሁኔታዎችን በተመለከተ የቀንና የሳምንት ሪፖርት ለጤና ጥበቃና ለአፍሪካ ህብረት እየላኩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በአካባቢው ያለውን ሁኔታም እንደተለመደው በንቃት እንዲከታተልና የሚያጠራጥር ነገር ሲያገኝም ለሚመለከተው አካል በፍጥነት እንዲያስታውቅ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

Related topics:
Ethiopia to deploy health professionals to Ebola-stricken ...
Ethiopian health workers arrive in Liberia to help fight Ebola
Ebola Scares Prevent Oklahoma Students ...
Kenya, Ethiopia boost anti-Ebola measures  
በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢቦላ ምርመራ እየተካሄደ ነው

No comments:

Post a Comment